Wednesday, December 16, 2015

የላኢላሃ ኢለላህ ትርጉምና መስፈርቶቹ



የላኢላሃ ኢለላህ ትርጉምና መስፈርቶች ምን ምን ናቸው?
ወንድሞችና እህቶች፤ ሁላችንንም አላህ ይምራን ካልን በኋላ፤ ላኢላሃ ኢለላህ ደግሞ የጀነት ቁልፍ መሆኗን ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል፡፡ በተለይ ደግሞ በሃገራችን ቃሉን ከመደጋገም ውጪ ብዙ ጊዜ ትርጉሙን በቁንፅል ብቻ ነው የተረዳነው የሚመስለን፡፡ ታዲያ ላኢላሃ ኢለላህ የጀነት ቁልፍ ነው ካልን፤ ቁልፍ ሆኖ ደግሞ ጥርሶች የሌሉት አይኖርም፡፡ ጥርስ ያለውን ቁልፍ አምጥተን ለመክፈት ከሞከርን ይከፍትልናል፤ ጥርስ የሌለውን ቁልፍ ይዘን ለመክፈት ብንሞክር ግን አይከፍትልንም፡፡ የላኢላሃ ኢለላህ መክፈቻ ቁልፍ ጥርሶች ደግሞ፤ ቀጥሎ የምንዘረዝራቸው መስፈርቶች ናቸው፡፡
ላኢላሃ ኢለላህ፤ ስምንት ያህል መስፈርቶች አሉት እያንዳንዳቸውን በማስረጃ እንመልከት፡
1.   ትርጉሙን ማወቅ፡

ትርጉሙን ማወቅ፤ ከመስፈርቶቹ የመጀመሪያው ነው፡፡ የላኢላሃ ኢለላህ ትርጉምም ባለፉት የተውሂድ ትምህርቶች እንደገለፅነው፤ ከአላህ ሌላ በትክክል ሊመለክ የሚገባው የለም በማለት፤ አምልኮንና መገዛትን ለአላህ ብቻ ማረጋገጥ ነው፡፡
በሱረት ሙሀመድ አንቀፅ19 አላህ (.) እንዲህ ይለናል
እነሆ፤ ከአላህ ሌላ አምላክ አለመኖሩንም እወቅ ይለናል፡፡ ይህ ማለት በሰማያትም ሆነ በምድር በትክክል ሊመለክ የሚገባው የለም ማለት ነው፡፡
 ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስም ረሱል (..)
ከአላህ ሌላ አምላክ እንደሌለ አውቆ የሞተ ሰው ጀነት ገባ ብለዋል፡፡ ስለዚህ ትርጉሙን ማወቁ አንዱ መስፈርት ነው ማለት ነው፡፡
2.   ያለምንም ጥርጣሬ ማረጋገጥ፡

ልባችን በዚህ በላኢላሃ ኢለላህ ላይ ምንም ጥርጣሬ ሳይኖረው ሙሉ ለሙሉ ማረጋገጥ አለበት፡፡ ከተጠራጠርን ግን ላኢላሃ ኢለላህን አፈረስን ማለት ነው፡፡
ለዚህም ማስረጃ፤ በሱረቱል ሁጁራት ቁጥር 15 ላይ አላህ እንዲህ ይለናል፦
 “(እውነተኞቹ) ሙእሚኖች፤ እነዚያ በአላህና በመልዕክተኛው ያመኑና ከዚያም ያልተጠራጠሩ ናቸው ይለናል፡፡
ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስም ረሱል (..) እንዲህ ብለዋል፦
 አንድ (የአላህ) ባርያ ከአላህ ሌላ አምላክ የለም ብዬ እመሰክራለሁ (የሚለውንና) እኔም የአላህ መልዕክተኛ መሆኔን ሳይጠራጠር፤ አላህን ተገናኝቶ፤ ከጀነት ሊታገድ አይችልም ብለዋል፡፡
3.   በፀጋ መቀበል፡

ከላይ የጠቀስናቸው ማወቅና ማረጋገጥ የሚሉት መስፈርቶች ብቻ በቂ አይደሉም፡፡ በተጨማሪም ላኢላሃ ኢለላህ የሚለው ቃል፤ ከእኛ የሚፈልግብንን ነገር ሁሉ፤ ከልብ በፀጋ መቀበልና በምላስም ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
አላህ (.) በሱረት አልሷፋት አንቀፅ 35 እና 36 ስለ አጋሪዎች (ሙሽሪኮች) ሲናገር እንዲህ ይለናል፦
 “እነሱ ከአላህ ሌላ አምላክ የለም በተባሉ ጊዜ ይኮሩ ነበር፡፡ እኛ ለባለቅኔ ዕብድ ብለን አማልክቶቻችንን የምንተው ነን እንዴ? ይሉም ነበር ይለናል፡፡
ታላቁ የቁርዐን ሙፈሲር ኢብኑ ከሲር በዚህ አንቀፅ ላይይኮሩ ነበርተብሎ የተጠቀሰውን ሲተረጉሙ፡
ልክ ሙእሚኖች በሚሉት ሁኔታ እናንተም ላኢላሃ ኢለላህን በሉ ሲባሉ ይኮሩ ነበር ማለት ነው ብለው አብራርተውታል፡፡
4.   መከተልና   መታዘዝ

ላኢላሃ ኢለላህ ያመላከተውን ነገር ሁሉ በመታዘዝ መተግበርና መከተል ያስፈልጋል፡፡ በሱረት አልዙመር ቁጥር 54 ላይ
 ወደ ጌታችሁ (በመፀፀት) ተመለሱ፤ ለእርሱም ታዘዙ፡፡ ይለናል
5.   እውነተኝነት
ይህም ላኢላሃ ኢለላህን ዝም ብሎ ላይ ላዩን ሳይሆን፤ በእውነት ከልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡በሱረት አልዐንከቡት ከቁጥር 1 እስከ 3 ድረስ አላህ እንዲህ ይለናል፦
 አሊፍ፤ ላም፤ ሚም፡፡ ሰዎቹ አምነናል በማለታቸው ብቻ፤ እነሱ ሳይፈተኑ የሚትተዉ፤ መኾናቸውን ጠረጠሩን?፡፡ እነዚያ ከነሱ በፊት የነበሩትን በእርግጥ ፈትነናል፤ እነዚያንም እውነት የተናገሩትን አላህ በእርግጥ ያውቃል፤ ውሽታሞቹንም ያውቃል፡፡ ይለናል፡፡ ረሱልም (..) እንዲህ ብለዋል፦
 “ከአላህ ሌላ አምላክ እንደሌለና ሙሀመድ የአላህ ባርያና መልዕክተኛ መሆኑን የሚመሰክር ማንም አይኖርም፤ አላህ እሱን በእሳት ላይ እርም ቢያደርገው እንጂ ብለዋል፡፡ እነዚህ ማስረጃዎች ከልብ፤ በእውነት መባል እንደሚገባው ያሳያሉ፡፡
6.   ማጥራት

ይህም መልካም ስራን፤ ከሽርክና ከሌሎች ግድፈቶች ሙሉ ለሙሉ ማፅዳትና ማጥራት ነው፡፡
በሱረት አልበይናህ አላህ (.) እንዲህ ይለናል፦
 “ለእርሱ (ለአላህ) ሃይማኖትን አጥሪዎች ኾነው፤ እንዲገዙት እንጂ አልታዘዙም ይለናል፡፡
 ቡኻሪ በዘገቡት ሀዲስ ረሱል (..) እንዲህ ብለዋል፦
 በእኔ ምልጃ (ሸፋዐህ) እድለኛ ሰው ማለት፤ ከልቡ ወይም ከነፍሱ አጥርቶ ላኢላሃ ኢለላይ ያለ ሰው ነው፤ ብለዋል፡፡
7.   መውደድ

ይህም ላኢላሃ ኢለላህን መውደድ ያስፈልጋል፡፡ ባለቤቶቿንም ማለትም ላኢላሃ ኢለላህን የተቀበሉና የሚተገብሩትን፤ መስፈርቶቿንም የጠበቁትን ሁሉ መውደድ ይገባል፡፡
ለዚህም ማስረጃ፤ በሱረት አልበቀራህ አንቀፅ 165 አላህ እንዲህ ይለናል፦
 “ከሰዎችም (ልክ) አላህን እንደሚወዱ የሚወዷቸው ኾነው፤ ከአላህ ሌላ ባላንጣዎችን (ጣዖታትን) የሚይዙ አልሉ፤ እነዚያ ያመኑትም አላህን በመውደድ (ከነርሱ) ይበልጥ የበረቱ ናቸው፡፡  ይለናል፡፡
ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ ረሱልም (..) እንዲህ ብለውናል፡
በውስጡ ሶስት ነገሮች ያሉበት ሰው የኢማንን ጣፋጭ ጣዕምን ያገኛል፡፡ አላህና መልዕክተኛው ከእነሱ ሌላ ካሉት ነገሮች ሁሉ እሱ ዘንድ የተወደዱ መሆን አለባቸው፡፡ ሰውን ሲወድ ለአላህ እንጂ ለሌላ መውደድ የለበትም፡፡ ልክ እሳት ውስጥ መወርወርን እንደሚጠላ ሁሉ፤ አላህ ካዳነው በኋላ፤ ወደ ክህደት መመለስን መጥላት አለበትብለዋል፡፡
8.   በጣዖታት መካድ፡
ይህም በጣዖታትና ከአላህ ሌላ በሚመለክ ነገር ሁሉ መካድና አላህ ጌታ እና ተመላኪ መሆኑን ማመን ነው፡፡
በሱረት አልበቀራህ አንቀፅ 256 አላህ (.) እንዲህ ይለናል፡
 “በጣዖትም የሚክድና በአላህ የሚያምን ሰው፤ ለእርሷ መበጠስ የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ ይለናል፡፡
 ረሱልም (..) “ ላኢላሃ ኢለላህ (ከአላህ ሌላ አምላክ የለም) ያለና፤ ከአላህ ሌላ በሚመለክ ነገር የካደ፤ ንብረቱም ሆነ ደሙም (ከመደፈር) እርም ይሆናልብለዋል፡፡

*********************************************************
2008E.C//2015G.C FANKIM ISLAMIC MEDIA NETWORK